ኤጀንሲው 187 ሚሊየን 395 ሺህ ብር ዋጋ ያላቸው አጎበሮችን እያሠራጨ መሆኑ ተገለፀ፡፡
February 7, 2020ፊውቸርድ ዜና
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ከGHSC-PSM /ኬሞኒክስ/ ጋር በመተባበር 3.1 ሚሊየን አጎበሮችን ለ3 ክልሎች ስርጭት መጀመሩን የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች ስርጭትና ተሽከርካሪ ስምሪት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሕመድ ከድር ጥር 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ገለፁ፡፡
ኤጀንሲው ከ3 ዓመት በፊት የተሠራጩትን አጎበሮች ቅያሪ እያካሄደ እንደሆነና አንድ አጎበር ለ3 ዓመት ብቻ የሚያገለግልና አጎበር ላይ የሚረጨው ኬሚካል ከ3 ዓመት በላይ ስለማያገለግል የቅያሪ ስራው እንደተካሄደ ተገልጿል፡፡
ካለፈው ሣምንት ጀምሮ የአጎበር ስርጭቱ በደቡብ ክልል ለሚገኙት ሠገን፣ ወላይታ፣ ምዕራብ ኦሞ፣ ሸካ እና ጋሞ ጎፋ ዞኖች እየተካሄደ መሆኑን አቶ አሕመድ አብራርተዋል፡፡
ይህ የአጎበር ስርጭት የመጀመሪያ ዙር መሆኑንና በቀጣይ ወራትም በቀሪ የደቡብ ክልል፣ ቤንሻንጉል እና ጋምቤላ ክልሎች ስርጭቱ እንደሚቀጥል አቶ አሕመድ አስረድተው አጎበሮቹ 187 ሚሊየን 395 ሺህ ብር ዋጋ እንዳላቸውና ወረዳ ድረስ ቀጥታ እንደተሠራጨ ተናግረዋል፡፡