ከዛሬ ጀምሮ ትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና ትላልቅ ስብሰባዎች በመላ ሃገሪቱ ለ15 ቀናት እንደሚዘጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ። =========================
March 17, 2020ፊውቸርድ ዜና
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ በዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ባሉበት ሆነው አስፈላጊው ክትትል ይደረግላቸዋል ብለዋል። አስፈላጊ ከሆነም አነስተኛ ስብሰባዎች በጤና ሚኒስቴር እውቅና እና ክትትል ሊደገፉ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ግብዓትን በተመለከተ ሳሙና አልኮልን ጨምሮ ሌሎች የንፅህና መጠበቂያዎች በስፋት እንደሚሰራጩም አስታውቀዋል።
እነዚህን የንፅህና መጠበቂያዎች ሰዎች በቀላሉ እንዲያገኟቸው በተለያዩ አካባቢዎች እንዲቀመጡ ይደረጋልም ነው ያሉት።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አሁን ላይ 5 መድረሳቸውን ጠቅሰው አምስተኛው ግለሰብ ከዱባይ የመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ትራንስፖርትን በተመለከተም በህዝብ ትራንስፖርት ላይ ያለውን መጨናነቅ ለመቀነስ የመንግስት ተሽከርካሪዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ በርካታ ተሽከርካሪ ያላቸው የግል ኩባንያዎች ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
የሃይማኖት ተቋማትን በተመለከተም ምዕመናን የሚሰበሰቡባቸውን ሁኔታዎች በጥንቃቄ ቢመለከቱ የሚል ምክር ሃሳብ አቅርበዋል።
ምንጭ፡- ጤና ሚኒስቴር