የመገኛ ቦታ ጠቋሚ መሣሪያ (GPS) የአንድ ዓመት የሥራ ሂደት ተገለጸ
የመገኛ ቦታ ጠቋሚ መሣሪያ (GPS) አፈጻጸም ሂደት ላይ የክምችትና ሥርጭት አስተዳደር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ከፍተኛ የአቅርቦት ሠንሠለት አማካሪ አቶ ዱፌራ ንግሣ ማብራሪያ ሰጡ፡፡
የመገኛ ቦታ ጠቋሚ መሣሪያ (GPS) የመድኃኒት እና ህክምና መሣሪያዎችን ለሚያሰራጩ 188 ከባድ ተሽከርካሪዎችና በ17 ቀላል ተሽከርካሪዎች ላይ መገጠሙን አቶ ዱፌራ ሐምሌ 13 ቀን በአዳማ በተዘጋጀው መድረክ ተናግረዋል፡፡
በአሁን ሰዓት ለከባድ መኪኖች 98.4 በመቶ፣ ለቀላል ተሽከርካሪዎች 68 በመቶ በአጠቃላይ በአማካይ 94 በመቶ መሣሪያው እንደተገጠመ አቶ ዱፌራ አስታውቀዋል፡፡
እስካሁን ባለው ሂደት መሣሪያው በአሶሳ የጠፉ መኪኖችን ለማስመለስ እንደተቻለ አማካሪው ተናግረዋል ፡፡
መሣሪያውን ለመተግበር የተዘጋጀ የሰው ኃይል እንዳለ ገልጸው በመመሪያው መሠረት የሚደረጉ ክትትልና የሚወሰዱ እርምጃዎች የመኪኖቹ አሽከርካሪዎች ባሉበት መሥሪያ ቤት ሥር እንደሚሆን ከዝግጅት ክፍሉ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
በባህርዳር፣ በነቀምት፣ በአዳማና በጅማ በሙከራ ደረጃ ለአንድ ዓመት እየተተገበረ መሆኑን አስታውቀው የመገኛ ቦታ ጠቋሚ መሣሪያው የሹፌር ሙሉ ስም፣ ስልክ፣ የመንጃ ፈቃድ ደረጃና የሚታደስበት ቀን እንዲሁም የመኪናውን ታሪክ ያካትታል ብለዋል፡፡
GPS የተሽከርካሪዎችን መገኛ ቦታ፣ እንቅሳቃሴያቸውን፣ የት፣ በምን ሰዓት እንዳለና የመኪኖች የነዳጅ አጠቃቀምን መረጃ እንደሚያሳይ ጠቁመዋል፡፡
ለተሽከርካሪው እንዲሁም ለአሽከርካሪው ደህንነት፣ ለሥራ ቅልጥፍና እና ለውሳኔ ሰጪዎች የተጣራ መረጃ ለማቅረብ ያስችላል ሲሉ አቶ ዱፌራ ተናግረዋል፡፡