የስራ ላይ ስጋቶቸን በመለየት በማስተካከያ እርምጃዎቹ ላይ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ
ኤጀንሲው ከደህንነት፣ ከስራ አካባቢ፣ ከመድኃኒት አቅርቦት ፍላጎት፣ ከገንዘብ እና ከቴክኖሎጂ ጋር የሚያጋጥሙ 35 የስራ ላይ አደጋዎች በመለየታቸው ማስተካከያና መከላከያ እርምጃዎች ላይ እንደሚሰራ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ ታህሣስ 18 ቀን 2013 ዓ.ም አስታወቁ፡፡በኤጀንሲው የአስር ዓመት ስትራቴጂክ አቅድ ከስራ ውሥብስብነት፣ በህብረተሰቡም ሆነ በመንግስት በኩል የመድኃኒት ፍላጎት መጨመር በመኖራቸው የሚታዩ ስጋቶች እንዳይከሰቱ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ኤጀንሲው የያዛቸውን ትልልቅ ግቦች ለማሳካት በመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱ ከስራው ፍሰት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ድረስ ያሉት እሴት በሚጨምሩ ተግባሮች የሚከሰቱ ስጋቶችን ISO 31000:2018 መስፈርት መነሻ ተደርጎ እየተሰራ እንደሆነ በኤጀንሲው ስትራቴጂክ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ አቶ ያሬድ ደለለኝ ተናግረዋል፡፡ የሚታዩም ሆነ የማይታዩ ስጋቶች በመኖራቸው በመድኃኒት አቅርቦቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚኖራቸው የማስተካከያ እቅድ መኖሩ፣ የትግበራ ቡድኑ ያላያቸውን ስጋቶች እንዲካተቱ አስተያየት ከመስጠት በተጨማሪም ቅርንጫፎች ከየራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተገናዘበ ስጋትን የመለየት እና የማካተት ስራ መስራት አንደሚገባ የጅማ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ አወል ጀማል ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ከ 300 ያለነሱ አቅራቢዎች ጋር የሚሰራ፣ ከ1000 በላይ መድኃኒቶችንና የህክምና ግብዓቶችን የሚያሠራጭ፣ ከ4200 በላይ ለሚሆኑ የጤና ተቋማት በ18 ቅርንጫፎቹ የሚያቀርብ፣ ከ 750 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የህክምና ግብዓቶችን የሚገዛ እንዲሁም ከ 300 በላይ የስራ ቅብብሎሽ ያለው በመሆኑ እና ከአለምአቀፍ ሁኔታዎች ጋር ተዳምሮ የስራ ላይ አደጋ የመሆን እድል እንዳላቸው ታሳቢ አድርጓል፡፡ አወል ሀሰን