የሹፌሮች ማትጊያ መመሪያ ለውይይት ቀረበ
የመድኃኒት እና የህክምና መሣሪያዎችን ለሚያሰራጩ የኤጀንሲው አሽከርካሪዎች የማትጊያ ጥቅማ ጥቅም የሚፈቅድ መመሪያ ሐምሌ 14 ቀን በአዳማ ከተማ ለውይይት ቀረበ፡፡
መመሪያው ከመገኛ ቦታ ጠቋሚ መሣሪያ (GPS) ከሚገኝ መረጃ እንዲሁም አስተዳደራዊ መስፈርቶችን መሠረት በማድረግ በሚገኝ ውጤት ለአሽከርካሪዎች የማትጊያ ክፍያ እንደሚሠጣቸው ታውቋል፡፡
የመድኃኒትና የህክምና መገልገያዎች ስርጭትና ተሽከርካሪዎች ስምሪት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አህመድ ከድር በኤጀንሲው የተዘጋጀው መመሪያ ሹፌሮች ከፍጥነት በላይ ማሽከርከርን፣ ከተፈቀደ ፍጥነት በታች መንዳትን፣ ነዳጅ ያለአግባብ መጠቀምንና መሰል መስፈርቶችን 60 በመቶ ለመመዘን ይጠቅማል ብለዋል፡፡
አቶ አህመድ በአሽከርካሪው ጥፋት የማድረስ አደጋ፣ የተሟላ ሰነድ ማቅረባቸውና በሚሰጡት አገልግሎት ላይ የሚቀርብባቸው የፅሁፍ ቅሬታ ወይም ማስጠንቀቂያ ከ40 በመቶ እንደመመዘኛ መስፈርት ይወሰዳል ብለዋል፡፡
አሽከርካሪዎች ከ(GPS) በሚገኘው መረጃና አስተዳደራዊ መስፈርቶችን መሠረት በማድረግ ከ90 በመቶ በላይ ለሚያመጡ 10ሺ ብር፣ ከ75 እስከ 89 በመቶ ውጤት ለሚያገኙ 7ሺህ ብር በሩብ ዓመት አንድ ጊዜ ያገኛሉ ተብሎ ተወስኗል፡፡
ከ60 እስከ 74 በመቶ ውጤት ለሚያመጡ አሽከርካሪዎች 3ሺህ ብር በሩብ ዓመት አንዴ እንደሚሰጥ አቶ አህመድ ተናግረው ከ59 በመቶ በታች ውጤት ለሚያመጡ አሽከርካሪዎች የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስበዋል፡፡
አሽከርካሪዎች ለሥራ ያላቸው ዝግጁነት ተመዝኖ በየወሩ 1ሺህ ብር እንደሚያገኙ መመሪያው ይገልጻል፡፡
አሽከርካሪዎች በየወሩ ለተሸከርካሪ ንፅህና መጠበቂያ እንደየመኪና ዓይነታቸው መጠን የሚሰጥ መሆኑን መመሪያው እንደሚገልጽ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
መመሪያውን ለማዘጋጀት በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ስድስት ተቋማት ተሞክሮ ተወስዶባቸዋል ሲሉ አቶ አህመድ ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ የኤጀንሲውን መድኃኒትና የህክምና መሣሪያዎች የሚያደርሱ አሽከርካሪዎች እና ከሁሉም ቅርንጫፍ በGPS ቁጥጥር የሚሰሩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡