የአቅርቦት ሠንሠለቱን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑ ተነገረ
የኤጀንሲው መድኃኒት አቅርቦት ሠንሠለት በተሻለ መንገድና በአጭር ርቀት እንዲሁም በፍጥነትና በቅናሽ ለማድረስ የሚያስችል ፕሮጀክት ለመተግበር እየተሠራ መሆኑን በማኬንዜ ሴቭ ፕሮጀክት የቡድን መሪ አቶ አበራ መንግሥቱ ተናገሩ ፡፡
የመንገድ አጠቃቀምን ውጤታማ ለማድረግ የመረጃ እጥረት እንዳለ አቶ አበራ ተናግረው የመድኃኒት ሥርጭት አገልግሎቱን ከመነሻ እስከ መድረሻ ለማስተካከል አሁን ካለው የኪሎ ሜትር ሽፋን ከ25 እስከ 35 በመቶ ከፍ ለማድረግ እንዳቀዱ አስታወቁ፡፡
ውጤታማ የአቅርቦት ሠንሠለት መንገድ ለመጠቀም የተዘጋጀው ፕሮጀክት ከመስከረም 2010 እስከ 2012 ዓ.ም ተግባራዊ ለማድረግ እንደታቀደ የቡድኑ መሪ ገልጸዋል፡፡
አቶ አበራ ፕሮጀክቱን ለመተግበር የአዳማ ቅርንጫፍ እንደተዘጋጀ ተናግረው በቀጣይ መቀሌ፣ ባሕርዳር፣ ሀዋሳ፣ ደሴ፣ ድሬዳዋ እና ጅማ ዝግጁ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
የአቅርቦት ሠንሠለቱን መንገድ ውጤታማ ማድረግ 48 በመቶ የነበረውን የቀጥታ ሥርጭት 75 በመቶ ከፍ ያደርጋል ተብሎ እንደታቀደ አቶ አበራ አስታውቀዋል ፡፡
ፕሮጀክቱ በዩኬ የልማት ድጋፍ እገዛ እንደሚደረግለት አስታውቀው የኤጀንሲው ከፍተኛ ኃላፊዎች ዕቅድ በመንደፍና ቅርንጫፎችን በማስተባበር አስተዋጾ እያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ቅርንጫፎች ትክክለኛ የመገኛ ቦታ አድራሻቸውን፣ የመድኃኒት ጭነት መጠናቸውንና መኪኖች በግቢያቸው ለምን ያክል ጊዜ እንደሚቆዩ ሙሉ መረጃ እንዲልኩ ጠይቀዋል፡፡