የአጎበር ስርጭት እየተካሔደ መሆኑ ተነገረ
በግሎባል ፈንድ ተገዝተው የቀረቡ አጎበሮች በሥርጭት ላይ እንደሚገኙ የፕሮግራም ስርጭት አስተባባሪ አቶ ሺፈራው በቀለ ዛሬ ከዝግጅት ክፍሉ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታወቁ፡፡
የአጎበሮች ብዛት 10.3 ሚሊየን በላይ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን አጎበሮች ከ576 ሚሊየን ብር በላይ ወጥቶባቸዋል ብለዋል፡፡
ስርጭቱ ከየካቲት 26 ጀምሮ መካሔዱን አስታውሰው አጠቃላይ በ220 ወረዳዎች ለማሰራጨት እቅድ እንዳለ አስታውቀዋል፡፡
አስካሁን ባለው ሂደት በዐማራ ክልል ለሚገኙ 36 ወረዳዎች ከ2.2 ሚሊየን በላይ አጎበሮች ተሰራጭተው መጠናቀቃቸውን አቶ ሺፈራው ተናግረዋል፡፡
8.6 ሚሊየን የሚሆኑት አጎበሮች በኦሮሚያ ክልል እየተሰራጩ እንደሚገኙ የታወቀ ሲሆን ስርጭቱን በቅርብ ቀን ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ እንዳለ ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በዓለም ጤና የአቅርቦት ሠንሠለት የግዢና አቅርቦት አስተዳደር በተገኘ ድጋፍ 5.5 ሚሊየን አጎበሮች ከግንቦት 25 ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ 12 ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን አቶ ሺፈራው ተናግረዋል፡፡
አቅራቢ ድርጅቶች በተያዘው መርሃግብር መሠረት ማቅረብ እንዳልተቻለ ተናግረው በኤጀንሲው በኩል አቅራቢ ድርጅቱ ያቀረበውን 1 ሚሊየን አጎበሮች ለዐማራ ክልል ከሰኔ 7 ጀምሮ አሰራጭተው ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡
በለጋሽ ድርጅቶች ተገዝተው የሚቀርቡት አጎበሮች በትግራይ፣ ደቡብ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ስር ለሚገኙ 143 ወረዳዎች እንደሚላኩ አመላክተዋል፡፡
ሥርጭቱ ከወደቦች በቀጥታ ወደ ሚፈለግበት ቦታ እንደነበር አቶ ሺፈራው ተናግረው በግሎባል ፈንድ የተገዙት አጎበሮች ወደብ ላይ በፍጥነት ማንሳት አለመቻሉ በጉዞ ላይ ያጋጠመው ችግር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡