የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት አለም አቀፍ የጥራት አመራር ስርአት መስፈርትን በማሟላቱ የአይ ኤስ ኦ/ISO, 9001:2015 እውቅናን አገኘ።
በእውቅና መርሀግብሩ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተገኝተው እንደተናገሩት አጠቃላይ የሀገሪቱን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የመድሀኒት እና የህክምና ግብአት አቅርቦት ሂደት መዘመን፣መሻሻልና መቀላጠፍ ወሳኝ መሆኑን አንስተው አሰራሩን ለማሻሻል እና ጥራትና ፈዋሽ መድሀኒትቶችን እንዲሁም ግብአቶችን ለተገልጋዬች ለማድረስ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ እና የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ሲሰሩ እንደነበር አስታውሰው በማኔጅመንቱ እና በጠቅላላው ሰራተኞች ብርቱ ጥረትም አለም አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ አይ ኤስ ኦ 9001:2015 እውቅና መገኘቱ አስደሳች ውጤት መሆኑን ገልጸዋል። በአጠቃላይ በጤናው ዘርፍ እየተተገበሩ ያሉ ሪፎርሞችም በፈተና ውስጥ ቢሆንም እንኳን ለማሳካት የመድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ያገኘው የጥራት ማረጋገጫ እውቅና ለሌሎች ተቋሞቻችን ምሳሌ ነውም ብለዋል። አሁንም በመድሀኒት አቅርቦት በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ እውቅናው ከፍተኛ ጉልበት የሚሰጥ በመሆኑ ለተሻለ ስራ መነሳሳት እንገሚገባ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ DQS group-country representative and lead Auditor የሆኑ አቶ ታደሰ ሰለሞንእንደተናገሩት GHSC-PSM/chemonics international በጋራ በመሆን በመድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና መስሪያቤት ፣አዳማና ሀዋሳ ቅርንጫፎች አለም አቀፍ የጥራት አመራር በሚጠይቀው መሰረት የኦዲት ስራ ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጸው በተገኘው የዘመናዊ አስራር የመድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና መስሪያቤት፣ አዳማ እና ሀዋሳ ቅርንጫፍ አይ ኤስ ኦ 9001:2015 የጥራት ማረጋገጫን መስጠቱን ተናግረዋል። ጥራቱም በየአመቱ የሚረጋገጥ መሆኑን ገልጸዉ ሁሉም የአገልግሎቱ ሀላፊዎች እና ሰራተኞች የተሰጠውን እውቅና ጠብቀው እንደሚያስቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። የእንኳን ደስ ያላቹ መልእክትም በማስተላለፍ የእውቅና ሰርተፊኬቱን ለአገልግሎቱ አመራሮች አስረክበዋል።የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በእውቅና ፕሮግራሙ ላይ እንደተናገሩት ተቋማቸው ጥራትና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድሀኒቶችን እና የህክምና ግብአቶችን ለጤና ተቋማት በሚፈለግ ደረጃ ለማድረስ፣ ውጤታማ እና ፈጣን ምላሽ ሰጪ አሰራሮችን ለመተግበር ሲሰራ እንደነበር ተናግረው ፣ የዛሬ እዉቅና ተቋማችን በሚፈለገው ልክ የተገልጋዩን ፍላጎት ስላሟላን ሳይሆን አቅርቦቱን ሰንሰለት ለማሻሻል መሰረተ የሚሆንን ነው ብለዋል። የጥራት አስተዳደር ስርአት በሶስተኛ ወገን ኦዲት ተደርጎ እና ተረጋግጦ የአይ ኤስ ኦ 9001:2015 የጥራት አመራር ስርአት ማረጋገጫ እውቅና በማግኘቱ መደሰታቸውን እና ከዋናው መስሪያቤት አንስቶ በሁሉም የተዋረድ መዋቅር የሚገኙ ሰራተኞች ልፋትና ውጤት መሆኑን ገልጸዋል። ሁሉም ሰራተኞኝ ለመድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ሁለንተናዊ መሻሻል እና የተልእኮ ስኬት በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ሀላፊው በህግ ማስከበር ሂደት ጉዳት ለደረሰባቸው የህክምና ተቋማትና ተገልጋዮች የመድሀኒት አቅርቦት እንዲኖር እያደረጉት ያለው ጥረትም ጉልህ ማሳያ ነው ብለዋል።እውቅና የተሰጠው የጥራት አስተዳደር ስርአትም ለዋናው መስሪያቤት፣ ለሀዋሳ እና ለአዳማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ በሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ተግባራዊ እንዲሆንም እንደሚሰራ ተናግረዋል። በቀጣይም ISO 28000(supply chain security) ለመተግበር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግሯል።።በእውቅና ፕሮግራሙ ከተወካዮች ምክርቤት፣ከጤና ሚኒስቴር፣ ከግዢ ኤጀንሲ፣ ከክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ፣ከአጋር አካላት እና ከመድሀኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ሀላፊዎች እና ሰራተኞች ተገኝተዋል። ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰራተኞች ፣ አመራሮች፣ አማካሪዎች እና ተቋማት እውቅናም ተሰጥቷል።