የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልጋሎ የ2014 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች፣ የኤጀንሲያችን ደንበኞች፣ ባለድርሻ እና አጋር አካላት፣ እንዲሁም የተቋማችን ሰራተኞች እና አመራሮች በቅድሚያ እንኳን ለ2014 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሰላም፣ በጤና አደረሳችሁ አደረሰን እያልኩ መጪው ዓመት የሰላም፣ የጤና እና የስኬት ዓመት እንዲሆንላችሁ በኢትዮጵያ #መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ስም ልባዊ ምኞቴን ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡የዜጎችን ጤንነት ለመጠበቅና ህይወትን ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የማይተካ ሚና እንዳለው ይታወቃል ፣ ይህም ፈዋሽነታቸውና ጥራታቸው የተረጋገጠ መሰረታዊና ህይወት አድን መድኃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ ለጤና ተቋማት በማቅረብ ለጤናው ዘርፍ ስኬታማነት ጉልህ ድርሻ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ በ2013 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎች የገጠሟት ቢሆንም ትላልቅ ስኬቶችም የተጎናጸፈችበት ዓመትም ነበር፡፡ አለም አቀፍ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ጨምሮ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች በተለይም በጤናው ዘርፍ ላይ ያሳደሩት ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ይሁንና የኤጀንሲው የቦርድ አመራሮች፣ የስራ ሀላፊዎች፣ ሰራተኞች፣ እንዲሁም የባለድርሻ እና አጋር አካላት ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ሀላፊነት ከነችግሮቻችን ለመወጣት አስችለውታል፡፡ ይህን ሁሉ ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ጫናን ተቋቁማችሁ በተሰማራችሁበት የስራ መስክ ኤጄንሲውን ስኬታማ እንዲሆን በብቃትና በትጋት የሚጠበቅባችሁን ሀላፊነት ለተወጣችሁ የተቋማችን አመራሮች ፣ሰራተኞች እንዲሁም ከጎናችን በመቆም በሀሳብና በገንዘብ ድጋፋ ላደረጋችሁልን የባለድርሻ እና አጋር አካላት ልባዊ ምስጋና አቀርባለው፡፡በ2014 የሥራ አመራር ቦርዳችን የሚሰጣቸውን አቅጣጫዎች መሰረት በማድረግ በባለፈው በጀት ዓመት የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን የበለጠ በማጎልበት፣ ድክመቶችን በመቅረፍ፣ አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር የአቅርቦት ሰንሰለቱን ውጤታማ በማድረግ የደንበኞችን እርካታ ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡ ስለሆነም አዲሱ ዓመት የመፈጸም አቅማችንን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ እና በላቀ ተነሳሽነት በመፈጸም እንዲሁም የአቅርቦት ሰንሰለቱን በማዘመን የይህወት አድን ና መሠረታዊ መድኃኒቶች አቅርቦት የበለጠ የምናሻሽልበት ፡ የኮቪድ-19ና ሌሎች ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ከምንጊዜውም በላይ ተቀናጅተን የምንቆጣጠርበትና መልካም ተሞክሮዎችን በሁሉም ተቋሞቻችን በማስፋት የምንተገበረበትና ተቋማችን በአድሰ አደረጃጀት ተዋቅረው በአዲስ መንፈስ ለላቀ ስኬት የምንተጋበት ሊሆን ይገባል፡፡ በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የሰላም ፣ የደስታ፣ የመተሳሰብ፣ የአንድነት፣ የብልፅግና፣ የጤና እና የፍቅር እንዲሆንልን እየተመኘሁ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች በድጋሜ መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆንላችሁ ልባዊ ምኞቴን እገልጻለሁ ፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!!!!