የደቡብ ክላስተር 3.2 ቢሊየን ብር ወጪ ያላቸው መድኃኒቶችን ማሠራጨቱን ገለፀ፡፡
3ተኛው የአቅርቦት ሠንሠለት መድረክ በጎንደር ከተማ በተካሄደበት ወቅት የደቡብ ክላስተር የ3.2 ቢሊየን ብር መድኃኒቶችን ማሠራጨቱን የሐዋሣ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘመን ለገሠ አስታወቁ፡፡
የደቡብ ክላስተር ሐዋሳ፣ አርባምንጭና ነገሌ ቦረና ቅርንጫፎችን ማቀፉንና 3 ክልሎች፣ 24 ዞኖች፣ 201 ወረዳዎች እንዳሉና በስሩም 932 ጤና ተቋማት ከኤጀንሲው አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን አቶ ዘመን ለገሠ ገልፀዋል፡፡
በክላስተሩ የ2.7 ቢሊየን ብር የጤና ኘሮግራም መድኃኒቶችና የ432 ሚሊየን ብር በመደበኛ ኘሮግራም መድኃኒቶች መሠራጨቱን አቶ ዘመን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ክላስተር በበጀት ዓመቱ ተሸከርካሪዎችን በጋራ ሲጠቀሙና መድኃኒቶችንም አዟዙረው በመጠቀም ከፍተኛ ተደጋግፎ የመስራት ባህል እንደነበራቸው አቶ ዘመን ተናግረዋል፡፡
ሌላው በ2011 በጀት ዓመት የሠራተኞች እርካታ የዳሠሣ ጥናት መካሄዱንና በሐዋሣ 70.1%፣ በአርባምንጭ 67.8% ፣ በነገሌ ቦረና 49.3% እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የተገልጋይ እርካታ መሠራቱንና ሐዋሣ 74%፣ አርባ ምንጭ 68.6% እና ነገሌ ቦረና 49.3% እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ሌላው በበጀት ዓመቱ “ዛሬ ያለ ትላንት ጎዶሎ ነው፤ ለቀድሞዎቹ እውቅና እንስጥ!” በማለት ለቀድሞ የአርባ ምንጭና የሐዋሣ ቅርንጫፍ ስራአስኪያጆች ሽኝት መደረጉን አቶ ዘመን በሪፖርቱ አመላክተዋል፡፡
በመጨረሻም አጠቃላይ ክላስተሩ በዱቤ ከሸጠው መድኃኒት ውስጥ 103.9 ሚሊየን ብር መሠብሠቡን ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት ሠምተናል፡፡