የፀጥታ ችግር በተከሰተባቸዉ አካባቢዎች የህክምና ግብዓቶችን ተደራሽ ለማድረግ ዉይይት ተካሄደ።
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የፀጥታ ችግር በተከሰተባቸዉ በአማራ ክልልና ሌሎች አካባቢዎች የህክምና ግብዓቶችን ከጤና ሚኒስቴር፣ ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከአገልግሎቱ ደሴ፣ ባህርዳርና ጎንደር ቅርንጫፍ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከአማራ ክልል የጤና ቢሮ ም/ኃላፊ ጋር ህዳር 5/2016 ዉይይት አድርገዋል፡፡
የህክምና ግብዓቶችን በፀጥታ ችግር ምክንያት ከዋና መስሪያ ቤት ወደ ባህርዳር ቅርንጫፍ በየብስ ትራንስፖርት ማድረስ አዳጋች በመሆኑ በጭነት አዉሮፕላን በመላክ ግብዓቶችን እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረጉ እንደሚገኙ የባህርዳር ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ አምሳሉ ጫኔ አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ሁኔታዉ እየተሻሻለ በመምጣቱ ዋናዉ መ/ቤት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከቅርንጫፎቻችን፣ ከጤና ቢሮ እንዲሁም ከጤና ተቋማት ጋር ያለዉን ግንኙነት በማጠናከር ስርጭቱን በሰፊዉ እና በቀጥታ ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን የመድኃኒት እና የህክምና መገልገያዎች ክምችት እና ስርጭት አስተዳደር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ በላቸዉ ገልፀዋል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ አበበ ተምትሜ እንደተናገሩት ከክልሉ ኮማንድ ፖስት ጋር በጋራ በመስራት ከቅርንጫፎች ጋር ግንኙነት በማድረግ አቅርቦቱ የተሳለጠ እንዲሆን እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዉ፤ ችግሮች በሚፈጠሩበት ወቅት ጤና ተቋማት ቅርንጫፎች ግብዓቶችን እስኪልኩላቸዉ ሳይጠብቁ ቀጥታ ወደ ቅርንጫፎች በመሄድ ግብዓቶችን ሊወስዱ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
#ማገልገል ክብር ነዉ
ሰላም ይደግ