የአዳማ ቅርንጫፍ 2500 ችግኞችን ተከለ
በመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ የአዳማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት “ዛፍ መትከል ተስፋን መትከል ነው” በሚል መሪ ቃል 2 ሺህ 500 ችግኞችን ተከለ፡፡
ቅርንጫፉ ሐምሌ 22 ቀን ባካሔደው የችግኝ መትከል መርሃ-ግብር ላይ ከ300 በላይ የቅርንጫፉ ሠራተኞች እንዲሁም ከዩኖፕስና ጃምቦ ኮንስትራክሽን ሠራተኞችና አመራሮች ጋር በመሆን ችግኞቹን ተክለዋል፡፡
የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ንጉሴ እንደገለጹት ችግኞችን በመትከል አካባቢን መንከባከብ ኤጀንሲው የተወከለበት ጤናን የመጠበቅ ተልዕኮ ጋር የሚሔድ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የችግኞቹ መተከል የግቢውን ልምላሜ ከፍ እንደሚያደርግ ተናግረው ችግኞቹ እንዲጸድቁ ኤጀንሲው የበኩሉን እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የተሳተፉት የዩኖብስ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ወርቅነሽ መኮንን የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አረንጓዴ ልማትን መሠረት ያደረገ መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
የችግኝ ተከላ ግቢውን አረንጓዴ ከማድረግ ባለፈ የተፈጥሮ ኡደት ሳይቋረጥ እንዲቀጥል የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም እየመጡ እንደሚንከባከቡ ቃል ገብተው ችግኝ መትከል የዘመቻ ሥራ እንዳይሆንና ሁሉም በወጥነት የችግኞቹ እንክብካቤ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የጃምቦ ኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ደበበ ሠይፉ በበኩላቸው “አረንጓዴ ልማት ላይ ያልተንተራሰ ልማት የእምቧይ ካብ” መሆኑን ተናግረው በመንግሥት ለአረንጓዴ ልማት የተሰጠው ትኩረት ሊደገፍ የሚገባው ነው ብለዋል፡፡
ድርጅታቸው ከኤጀንሲውና ከዩኖብስ ጋር በመሆን ችግኞችን በመትከል አካባቢውን እንዳለማ አስታውሰው የዛሬውም የችግኝ ተከላ “ለአረንጓዴ ልማት አርአያና ተምሳሌታዊ የሚሆን” ነው ብለዋል፡፡
ችግኞቹ ከአካባቢው የአየር ጸባይ ጋር ተስማሚ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን 2ሺ 100 ችግኞች ከግብርና ቢሮ በተመደበ ቀሪው 450 ደግሞ በግዢ መቅረባቸውን በነበረን ቆይታ ሰምተናል፡፡
ችግኞቹ የተተከሉት የቅርንጫፉ ኢንሲኔሬተር በሚገኝበት ግቢ ውስጥ እና በግቢው ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች መሆኑን የዝግጅት ክፍሉ ተመልክቷል፡፡