ኤጀንሲው ለፖሊዮ ቅድመ መከላከል ዘመቻ የክትባት መድኃኒቶችን እያሠራጨ እንደሆነ አስታወቀ፡፡
November 7, 2019ፊውቸርድ ዜና
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ከሕዳር 12–15/2012 ዓ.ም. ለሚካሄደው የፖሊዮ ቅድመ መከላከል ዘመቻ የክትባት መድኃኒቶችን እያሠራጨ መሆኑን የክትባት ፕሮግራም መድኃኒት ክትትል ባለሞያ ወ/ት ናዲያ ሲራጅ ዛሬ ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ገለጹ፡፡
የፖሊዮ ቅድመ መከላከል ዘመቻ በአገር አቀፍ ደረጃ በሕዳር ወር አጋማሽ እንደሚካሄድ ባለሞያዋ ገልፀው የክትባት መድኃኒቶቹን በኤጀንሲው 15 ቅርንጫፎች አማካኝነት እያካሄደ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ባለሙያዋ ክትባቱ ከ5 ዓመት በታች ላሉ 5 ሚሊየን 373 ሺህ 171 ሕፃናት እንደሚሠጥ ገልፀው ኤጀንሲውም 5 ሚሊየን 977 ሺህ 203 የክትባት መድኃኒቶችን እያሠራጨ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ወ/ት ናዲያ የክትባት መድኃኒቶቹ ከ31 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው መሆኑን አስታውቀው ሕብረተሠቡ ለክትባቱ ትኩረት ሠጥቶ ሕፃናትን ማስከተብ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡