የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የላቦራቶሪ አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል በ2018 በጀት ዓመት 295 የCBC (Complete Blood Count) ማሽኖችን ለጤና ተቋማት ለማቅረብ ማቀዱን አስታወቀ።
የዚሁ ዕቅድ አካል የሆነው የመጀመሪያ ዙር የ81 ማሽኖችና የሪኤጀንቶች ርክክብ ጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም በአገልግሎቱ ዋና መሥሪያ ቤት ተከናውኗል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬሕይወት አበበ፣ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ፍሬሕይወት አበበ በወቅቱ እንደገለጹት፣ በጤናው ዘርፍ የተጀመረው ሪፎርም ውጤት እያመጣ ሲሆን፣ በተለይም እነዚህ ማሽኖች የእናቶችና የሕፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ያግዛሉ።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፣ ማሽኖቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ለጤና ቢሮዎች እየቀረቡ መሆኑንና ቀሪዎቹ 214 ማሽኖች እስከ ሰኔ 2018 ዓ.ም ድረስ ለተቋማቱ እንደሚዳረሱ አረጋግጠዋል።
እነዚህ ዘመናዊ ማሽኖች ለአጠቃቀም ምቹ ከመሆናቸው ባለፈ፣ በምርመራ ወቅት ትክክለኛ መረጃን በአጭር ጊዜ ውስጥ መስጠት መቻላቸው ለሕክምናው ሂደት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።
#ማገልገል ክብር ነው!
በአማኑኤል ወርቃየሁ