በሕክምና ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለት ላይ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኘው የኩህኔ ፋውንዴሽን (Kuehne Foundation) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር ኒክላስ ዊልምኪንግ፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ፤ ስለ ተቋሙ አወቃቀር፣ ስለ ኢትዮጵያ የጤና መረጃ ፍሰት እና ስለ አቅርቦት ሰንሰለቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ (End-to-End) ሂደት ለጎብኚዎቹ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል። በተለይም ተቋሙ ተግባራዊ ያደረገው የተቀናጀ የዲጂታላይዜሽን ስርዓት በአሰራር ላይ ያመጣውን መሠረታዊ ለውጥ በዝርዝር አስረድተዋል።
የኩህኔ ፋውንዴሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር ኒክላስ ዊልምኪንግ በበኩላቸው፣ አገልግሎቱ ያለውን ተቋማዊ አቋምና ዘመናዊ አሰራር አድንቀው፤ በቀጣይም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን ለይተው ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተፈሪ ገንድፍ እንደገለጹት፤ ድርጅታቸው በ2026 በኢትዮጵያ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ለመስራት ያቀዳቸው በርካታ ተግባራት አሉ። ይህ ጉብኝትም በቀጣይ በሚደረጉ ድጋፎች ዙሪያ ከበላይ ኃላፊዎች ጋር ለመወያየት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።
የልዑካን ቡድኑ በመጨረሻም የተቋሙን የመድኃኒት መጋዘኖች በአካል ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
#ማገልገል_ክብር_ነው!
ማኅሌት አበራ