የመድኃኒቶችን መረጃ ከአምራች እስከ ተጠቃሚ ድረስ ያለውን ጉዞ (Visibility) ግልጽ የሚያደርግና ዘመናዊ የአቅርቦት ሥርዓትን የሚያረጋግጥ የባርኮድ ሲስተም ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጠ።
ዘመናዊና የተሳለጠ የሕክምና ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለት ለመገንባት እንዲሁም የክትትልና ቁጥጥር አሰራርን ለማሻሻል ያለመ የውይይት መድረክ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን (EFDA) መካከል ጥር 26 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሂዷል።
የመረጃ መናበብ (Master Data maping) ወሳኝ እንደሆነ በዉይይቱ የተገለፀ ሲሆን ቴክኒካዊና የሲስተም ትግበራዉን የሚገነቡ የICT ቡድኖችም እንደሚዋቀሩ ተገልጿል።
የአገልግሎቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ንጉሴ እንዳሉት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ያለዉን የዉስጥ አቅም በቴክኖሎጂ በመደገፍ ማህበረሰቡን ለማገልገል ከመቼዉም ጊዜ በላይ በቁጭትና በፍጥነት እየሰራ ሲሆን ከኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ጋርም የባርኮዲንግ አተገባበር ልምድ ለመካፈልና በቅንጅታዊ አሰራር ሀገራዊ ትልምን ለማሳካት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸዉን ተናግረዋል።
የባለስልጣኑ የመድኃኒት ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም ወልዴ በበኩላቸዉ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለማዘመን ከአገልግሎቱ ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን አስታዉሰዉ ቋሚ የግንኙነት ጊዜ በማስቀመጥ የተጀመሩ ስራዎች እየተገመገሙ ዉጤታማ ስራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
#ማገልገል ክብር ነዉ
አማኑኤል ወርቃየሁ