አገልግሎቱ ስለ ተቋሙ የፋይናንስ አስተዳደር ፤ ተሰብሳቢ ሂሳብ ፤ ስለ አዲሱ የመረጃ ስርዓት SAP እና ሂሳብ አዘጋግ ዙሪያ ከቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆችና አስተባባሪዎች ጋር በአዳማ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ወቅት የመረጃ ግልፀኝነት ፣ የክፍያ ፍጥነት ማሻሻል እና የገንዘብ ፍሰት ጥንካሬ ላይ ትኩረት ተደርጓል። ይህም የመድኃኒት ቀጣይነት አቅርቦትን ለማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑ ተጠቅሷል።
ተቋሙ የተሻለ አፈፃፀም ለማምጣት እና የተሰብሳቢ ሂሳብ ክትትልን ለማጠናከር በቀጣይ በመናበብ በቅርብ እንደሚሰራ ተገልጿል።
የፋይናንስ ስርዓታችንን በማሻሻል በአለም አቀፍ ተቋማት ደረጃ ተዓማኒነታችንን ከፍ ማረግ አለብን ያሉት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ ግልፀኝነትን ማስፈን እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአገልግሎቱ የጤና ስርዓት ማጠናከሪያና የፋይናንስ አስተዳደር ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ በላቸዉ የ2016 እና 2017 ዓ.ም ተሰብሳቢ ሂሳብን በጥልቀት የገመገሙ ሲሆን ፤ ያልተጠናቀቀ ተሰብሳቢ ሂሳብ (Backlog) ተቋሙ በጀመረዉ ሪፎርም በፍጥነት መጠናቀቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ሁሉም ቅርንጫፍ ወጥና የተናበበ መረጃ ሊኖረዉ እንደሚገባ የገለፁት ም/ዋና ዳይሬክተሩ የፋይናንስ ስርዓቱ እየተገበረ ያለዉን የተቀናጀ የመረጃ አያያዝ ስርዓት ERP/SAP አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የዉይይቱ ተሳታፊዎችም የመረጃ ግልፀኝነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን ባጠረ ጊዜያት ዉስጥ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን አጠናቀዉ የተቋሙን ተዓማኒነት እንደሚያረጋግጡ ተናግረዋል።
#ማገልገል ክብር ነዉ
አማኑኤል ወርቃየሁ