የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በ2030 በአፍሪካ ፈጣንና ቀልጣፋ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ያለው ተቋም ለመሆን የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች በበለጠ ጥንካሬና ቁርጠኝነት ሊቀጥሉ እንደሚገባ የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ በላቸው ገለጹ።
አቶ ታሪኩ ይህንን የገለጹት ከሐምሌ 17 እስከ 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ከአገልግሎቱ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ነው።
በመድረኩ ላይ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ የቀጣይ ሦስት ዓመታት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በአግባቡ ተተንትኖ እስከ ታችኛው የሥራ አስፈጻሚ ድረስ በመውረድ ሁሉም ሠራተኞች የተቋሙን ራዕይ ለማሳካት በትኩረት እንዲሠሩ አሳስበዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ከዕቅድ ጋር የተጣጣመ የበጀት አጠቃቀም ሥርዓትን ማጠናከር የስትራቴጂካዊ ዓላማዎችን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም የተሰብሳቢ ሂሳብ አስተዳደር ለተቋሙ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሁለተኛውን የመድኃኒት አቅርቦት ልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ (PSDIP II) በተሳካ ሁኔታ ለማስፈጸም ሁሉም የአገልግሎቱ አመራሮችና ሠራተኞች ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በበኩላቸው የአገልግሎቱ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች፣ ተቋሙ በ2030 በአፍሪካ ፈጣንና ቀልጣፋ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ያለው ተቋም የመሆን ራዕዩን ለማሳካት የተዘጋጀውን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በተግባር ለማዋል ያላቸውን ሙሉ ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
አስኪያጆቹ አክለውም፣ በየቅርንጫፉ የሚተገበሩ የሪፎርም ሥራዎችን በተጠናከረ መልኩ በመተግበር የመድኃኒት ተደራሽነትን፣ የአገልግሎት ቅልጥፍናን እና ጥራትን በማሻሻል የተቋሙን ራዕይ እውን ለማድረግ ከዋናው መሥሪያ ቤት ጋር በተቀናጀ መንገድ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
#ማገልገል_ክብር_ነው