ባለፉት አምስት አመታት ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ የመድኃኒትና የህክምና ግብዓቶች አቅርቦት ስርዓት በማጠናከር የጤና ዘርፉን ለማሻሻል እና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ተልዕኮ ለማሳካት ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ፣ ትብብርና ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋናና የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቷል ።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞ ባደረጉት ንግግር፤ ተቋሙ ከስድስት ዓመታት በፊት በርካታ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ይነሱበት የነበረ መሆኑን አስታውሰው ፣ በአመራሩ ከፍተኛ ትጋት እና በተወሠደው ቁርጠኝነት አሰራሩንና ስሙን በመቀየር ለሌሎች የመንግሥት ተቋማት አርአያ መሆን የሚችል ነው ብለዋል።
አክለውም የቋሚ ኮሚቴው አባላት በቀጣይ በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ የአገልግሎቱ አምባሳደር ሆነው እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል ።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፤ ቋሚ ኮሚቴው ያቀረባቸው ጠንካራ ጥያቄዎች ተቋሙ የኦዲት ሥርዓቱን እንዲያስተካክልና የፍላጎት ትንበያዎችን በትክክል እንዲያከናውን ትልቅ ድጋፍ እንደሆናቸው ገልጸዋል።
አዋጁ መፅደቁ ተቋሙ ትልቅ የመድኃኒት አቅርቦት ሠንሠለት አቅም እንዲገነባ ማድረጉን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህም የግዥ ሥርዓቱን ዲጂታላይዝድ በማድረግ፣ የሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች ድርሻ እንዲያድግ እና ውልን መሠረት ያደረገ የአቅርቦት ሥርዓት(CDSS) መዘርጋት መቻሉን ገልጸው ለቋሚ ኮሚቴው ምስጋና አቅርበዋል።
"የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ፣ ማህበራዊ ልማት ፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ባለፉት 5 ዓመታት ላደረጋችሁልን የላቀ ድጋፍ፣ በተለይም የአገልግሎቱን አዋጅ በማውጣት፣ አስፈላጊውን የቁጥጥር እና የፖሊሲ አቅጣጫ በመስጠት ላበረከታችሁት ገንቢ አስተዋጽኦ ከልብ እናመሰግናለን " ብሏል የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት
በመጨረሻም የቋሚ ኮሚቴው አባላት የአገልጎሎቱን አዲስ ሕንፃ ልዩ ልዩ የስራ ክፍሎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
#ማገልገል ክብር ነው!