የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳለው አስማማው እንደገለጹት፣ የደንበኞች ቀን መድረክ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻልና በተቋሙና በደንበኞች መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር ጉልህ ሚና አለው። በተለይም የአገልግሎት መጠበቂያ ጊዜን ለማሳጠርና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የኦንላይን የግዥ ሥርዓት (Online Ordering) እየተጠቀመ መሆኑን ገልጸዋል። ደንበኞችም ሥርዓቱን በአግባቡ በመጠቀም የአገልግሎት ቅልጥፍናን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።
የማርኬቲንግና ደንበኞች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ገዳምነሽ አስፈራው በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የአገልግሎቱ ቅርንጫፎች ሰፊ የአቅርቦት አቅም እንዳላቸው ጠቁመው፣ በደንበኞች ቀን መድረክ የሚነሱ ሐሳቦችና ጥቆማዎች የተቋሙን ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች ለማዘጋጀትና ለማሻሻል ጠቃሚ ግብዓት እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
በመድረኩ የአገልግሎቱ ዳይሬክተሮች፣ የፌዴራል ሆስፒታሎች ተወካዮች፣ የተመረጡ የአዲስ አበባ ሆስፒታሎች፣ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ተወካዮች እንዲሁም የቅርንጫፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
ተሳታፊዎቹ የተቋሙን ዲጂታል አሠራሮችና ከማዕከል ወደ ቅርንጫፍ ያለውን የሥራ ፍሰት በአዎንታዊነት ገምግመው፣ በመሠረታዊ መድኃኒቶች፣ በተለይም በአእምሮ ሕመምና በካንሰር ሕክምና መድኃኒቶች ላይ የሚታየውን የአቅርቦት መቆራረጥ ለመፍታት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል። በተጨማሪም የአንዳንድ የአእምሮ ሕመም መድኃኒቶች ዋጋ እንዲገመገምና ውል የተገባለት የአቅርቦት ሥርዓት (CDSS) አፈጻጸም እንዲጠናከር ጥቆማ አቅርበዋል።
ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳለው አስማማው፣ የደንበኞችን አገልግሎት ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ ዘመናዊ አሠራሮችን ከመዘርጋት ባሻገር የሕክምና ግብዓቶች በበቂ መጠን እንዲቀርቡ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። የኦንላይን የግዥ ሥርዓትን በመጠቀምና በትብብር በመሥራት የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻልም አስረድተዋል።
ወ/ሮ ገዳምነሽ አስፈራው በበኩላቸው፣ መሠረታዊ መድኃኒቶች በበቂ ሁኔታ እንዲቀርቡ አገልግሎቱ ከሚመለከታቸው የጤና ዘርፍ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። የግብዓት ግዥና የፋይናንስ ሥርዓቱ የበለጠ የተረጋጋ እንዲሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል።
በተደረገው የሦስት ወራት ጥናት መሠረት፣ የጤና ተቋማት ከሌሎች አቅራቢዎች ይልቅ ከአገልግሎቱ የሕክምና ግብዓቶችን ሲገዙ 3.35 ቢሊዮን ብር ሊቆጥቡ እንደሚችሉ የማርኬቲንግ ክፍል ጥናት ያመላከተ ሲሆን ፤ የጤና ተቋማት የግዥ ወጪን ለመቀነስና ያላቸውን ሀብት በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም ከአገልግሎቱ ጋር የሚያደርጉትን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ ያሳያል።
#ማገልገል ክብር ነዉ