በጉባኤው የEPSS ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎን ጨምሮ የጤና ዘርፍ አመራሮች፣ የሙያ ማህበራት ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የልማት አጋሮች፣ የፋርማሲ ባለሙያዎችና የተጋበዙ እንግዶች ተሳትፈዋል።
ጉባኤውን በይፋ ያስጀመሩት ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ፣ የፋርማሲ ባለሙያዎች ጤናማ ማህበረሰብን በመገንባት ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል። የፋርማሲ ሙያ የመድኃኒት አቅርቦትን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን የሕይወት ጥበቃ፣ የሕክምና ጥራት፣ የታካሚዎች ደህንነትና የጤና ሥርዓቱን በማጠናከር የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ጥራት ያለው መድኃኒት በወቅቱና በትክክለኛው ቦታ ማድረስ የEPSS ብሔራዊ ተልዕኮ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንን ተልዕኮ ለማሳካት የፋርማሲ ባለሙያዎች በዲጂታል ለውጥ፣ በፈጠራ፣ በምርምርና በትብብር የለውጥ መሪዎች መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም በጉባኤው የሚካሄዱ ውይይቶችና የሚቀርቡ ምክረ ሐሳቦች ከውይይት ወደ ፖሊሲ፣ ከፖሊሲ ወደ ተግባር በመሸጋገር ለሕዝብ ጥቅም እንዲውሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳንኤል ዋቅቶሌ በበኩላቸው፣ በጉባኤው የሚካሄዱ ውይይቶች የሚያፈልቋቸው ምክረ ሐሳቦች ለመንግሥትና ለባለድርሻ አካላት ቀርበው በሀገሪቱ የጤናና የፋርማሲ ዘርፍ ሪፎርሞችን ለማጠናከር ጠቃሚ ግብዓት እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
በጉባኤው የተለያዩ የሕክምናና የፋርማሲ ግብዓት አቅራቢ ድርጅቶች ምርቶቻቸውንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎቻቸውን በኤግዚቢሽን አቅርበዋል። ኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት (EPSS) ለ46ኛው ዓመታዊ ጉባኤ የፕላቲኒየም ደረጃ ስፖንሰር በመሆን ለፋርማሲ ሙያ እድገትና ለሀገሪቱ የጤና ሥርዓት መጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል።
ጉባኤው በፋርማሲ ሙያ ላይ የሚኖሩ አዳዲስ አቅጣጫዎች፣ የዲጂታል ለውጥ፣ የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓት ማሻሻያዎች፣ የሙያ ልማትና የጤና ሥርዓቱን ማጠናከር በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ተጠናቋል።
#ማገልገል_ክብር_ነው