የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መና መኩሪያ ዝግጅቱ በአገልግሎቱና በጤና ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከርና የአቅርቦት ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት ጠቃሚ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም ውል የተገባለት የአቅርቦት ሥርዓት ውጤታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የሕክምና ግብዓቶችን በጥራት፣ በተመጣጣኝ ዋጋና በዘላቂነት ለጤና ተቋማት ለማቅረብ የሚደረጉ ጥረቶች፣ የአቅርቦት ተግዳሮቶችና የደንበኞች ፍላጎቶች ላይ ውይይት ተካሂዷል። የማርኬቲንግና ደንበኞች አስተዳደር ዳይሬክተር ወ/ሮ ገዳምነሽ አስፈራው የአቅርቦት ሥርዓቱን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ለደንበኞች ፍላጎት ፈጣን ምላሽ ሰጪ ለማድረግ በስትራቴጂያዊ አተገባበርና በተቀናጀ አሠራር ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንድነት አሰፋ መድረኩ የደንበኞችን ፍላጎትና አስተያየት ለመረዳት፣ በአቅርቦት ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታትና የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ ያለውን ፋይዳ አጉልተው ገልጸዋል። ቅርንጫፉ ከደንበኞቹ ጋር በቅንጅት በመሥራት የተሻለና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በውይይቱ የደንበኞችን አስተያየት ወደ መፍትሔ በመቀየር የአቅርቦት ሥርዓቱንና የተቋማትን ትብብር ማጠናከር ላይ ትኩረት ተደርጓል። የጤና ተቋማት ተወካዮችም የውል አቅርቦት ሥርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን ቅንጅት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በዕለቱም በጥሩ አፈጻጸም ለተለዩ ሆስፒታሎች ዕውቅና ተሰጥቷል።
#ማገልገል ክብር ነዉ